Error message

Deprecated function: Array and string offset access syntax with curly braces is deprecated in include_once() (line 1389 of C:\xampp\htdocs\tourism\includes\bootstrap.inc).

 “አዲስ እሳቤ ለቱሪዝም” በሚል መሪ ቃል በሀገራችን ለ35ኛ ጊዜ በክልላችን ለ28 ጊዜ ለምናከብረው የዓለም የቱሪዝም ቀን በዓል እንኳን አደረሳችሁ፡፡
 
ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊ እና በሰው ሰራሽ የቱሪዝም መስህቦች እምቅ አቅም አኳያ ከዓለም ግንባር ቀደም የቱሪስት መዳረሻ መሆን የሚትችል ሀገር ናት። ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርስ ያላት ሀገር ናት። በተባባሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የተመዘገቡ የኢትዮጵያ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች የአክሱም ሃውልቶች፣ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያን፣ የጎንደር ፋሲል ግምብ፣ የሐረር ጆጎል ግንብ፣ የጢያ ትክል ድንጋዮች፣ የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ፣ የኮንሶ ሰው ሰራሸ መልከዓ ምድር፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ እና የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፤ እንዲሁም በማይጨበጥ የባህል ቅርስነት የመስቀል የደመራ በዐል፣ የሲዳማ የዘመነ መለወጫ ፊቼ ጨምበላላ እና የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ላሉን ሀብቶች ህያው ምስክር ናቸው።
 
ሌሎች ለመመዝገብ በሂደት ላይ ያሉም የሚገኙ የጌዴኦ ባህላዊ  መልከዓ ምድር፣ የባሌ ተራራች ብሄራዊ ፓርክ፣ የድሬ ሼህ ሁሴን መስጊድ፣ የሶፍ ኡመር ዋሻ፣ የመልካ ቁንቱሬ እና ባቺልት የአርኪዮሎጂ ስፍራዎች እና በማይዳሰስ ቅርስ ለማስመዝገብ የተጀመረው የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ”ን ጨምሮ በርካታ ባህላዊ ሀብቶች የሚገኙባት ሀገር ናት ኢትዮጵያ።
ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የአረቢካ ቡና ዝርያ፣ የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ጥቁር አባይ፣ የኤርታአሌ እሳተ ገሞራ ሀይቅና የዓለማችን እጅግ ረባዳና ሞቃት ስፍራ ዳሎልም የሚገኘውም በኢትዮጵያ ነው። በርካታ ለመዝናናት አመቺ የሆኑ የስምጥ ሸለቆ ሃይቆችና ፍል ውኃዎች፣ እንዲሁም የዱር እንስሳት ፓርኮችና ጥብቅ ቦታዎች ያሏት ሀገር ናት። በመሆኑም ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፤ ሰው ሰራሽና ባህላዊ ቅርሶችን በዩኔሰኮ በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚዋ አገር ብትሆንም የአገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ግን የሚገባውን ያህል አላደገም።
 
በሀገራችን ካሉ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ተመረጭ የሆነው ክልላችን ደቡብ ብሔሮች ብሐየረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በርካታ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶች መገኛ ክልል ነው፡፡
የብሔረሰቦች ሙዚየም በመባል የሚታወቀው ክልላችን ቱባ የባህል ሀብቶችና ድንቅ የተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለ የቱሪዝም ትልቅ አቅም ያለው ክልል ነው። በክልላችንም ሆነ በሀገራችን የሚገኙ ታሪካዊ ተፈጥሯዊና ባህላዊ ሀብቶችን በመጠቀም ለቱሪዝም ዘርፍ ተወዳዳሪ በመሆን ማግኘት የሚገባንን ያህል ጥቅም ለማግኘት ከሰራን ቱሪዝም ባለተስፋው የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው፡፡ ስለሆነም በክልላችን የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን የማስተዋወቅና የቱሪዝም ቀን የማክበር ዓላማችን ያለንን ሀብት በሚመጥን ደረጃ በማልማት የቱሪዝም ዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ነው።
 
በክልሉ የሚገኙ የብሔሮችና ብሔረሰቦች የብዝሀ ባህል መገለጫ ከሆኑ ዕሴቶች መካከል አንዱ የባህላዊ ምግብና መጠጥ እንዲሁም አዘገጃጀት ሥርዓቱ የክልላችን ህዝቦች የቱሪስት መስህብ መሆን ከሚችሉ ሀብቶች አንዱ ነው፡፡ በሁሉም ብሔረሰቦች የሚዘጋጁ ባህላዊ ምግቦች ልዩ ጣዕም ያላቸውና ለጤና ተስማሚ ከመሆናቸውም በላይ ባህላዊ የአዘገጃጀትና የአመጋገብ ሥርዓቱ ለቱሪዝም የጎላ ፋይዳ ያለውና የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስብ ነው፡፡ ፓሎታ የእህል ምርትን በመሬት ዉስጥ ለረጅም ጊዜ ማቆየት የሚችል ድንቅ ጥበብ፣ የዶርዜ ባህላዊ ሽመና ስራ፣ ከእንጨትና ብረታብረት የሚሰሩ የእጅ፣ የአንገትና የእግር ጌጣጌጥና ቅርጻቅርጽ ስራዎች፣ የሽክላ ስራ ውጤቶች እንዲሁም በሳር የሚሰሩ የአለላና የስንደዶ ስራ ውጤቶች የመሳሰሉ የዕድ ጥበብ ምርቶች ከአዘገጃጀት ጀምሮ እስከ አጠቃቀም ድረስ ያለው ሂደት በክልላችን ከሚገኙ ዕምቅ የቱሪዝም መስህቦች ናቸው፡፡ የክልሉ ብሔር ብሔረሰቦች የየራሳቸው የሆነ የተለያዩ ባህላዊ ጫዋታዎች፣ ጭፈራዎችና የሙዚቃ መሳሪያዎች ያሉዋቸው ሲሆን አንዳንዶቹ የሙዚቃ መሳሪያዎች አብዛኛዎቹ ብሔረሰቦች የሚጋሯቸው የጋራ እሴቶች መሆናችው እንደተጠበቀ ሆኖ በዲራሼ ብሄረሰብ ዘንድ ተወዳጁ ፊላ አንድም የሙዚቃ መሳሪያ፣ በሌላ በኩል በመሳሪያ ብቻ የተቀነባበረ ሙዚቃና የሚወክል ከመሆኑም በላይ ፊላ ውዝዋዜም ነው፡፡ እነዚህ ሶስቱ ተዋህደው የሚፈጥሩት ህብር አንድነትን፣ መደማመጥን፣ መግባባትን፣ መናበብን በአጠቃላይ ልዩ የሙዚቃን መሳጭ ጥበብ ይፈጥራሉ፡፡ የክልላችን ህዝቦች የሚታወቁባቸው ባህላዊ ቤቶች የማህበረሰቡን አገር በቀል እውቀት በጉልህ ከማሳየታቸው ባሻገር ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ገጽታቸው በቱሪስቱ የሚወደዱና ተዘውትረው የሚጎበኙ ናቸው፡፡
 
በክልሉ የሚገኙ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የማንነታቸው መገለጫ የሆነ ውብና ማራኪ ጭፈራና ልዩ ልዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ከበዓለ አከባበር፣ ከጋብቻና ለቅሶ ሥርዓት እንዲሁም ከተለያዩ ማህበራዊና ባህላዊ ሁነቶች ጋር በጽኑ የተቆራኙና ተዘውትረው የሚከወኑ ናቸው፡፡  ኢቫንጋዲ በሀመር ብሄረሰብ ‹‹የምሽት ጭፈራ›› የሐመር ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች ብቻ የሚሳትፉበት ባህላዊ ጭፈራ በአዝመራ ወቅት በሥራ የደከመን አእምሮና አካል ለማዝናናት ሲባል የሚደረግ ባህላዊ ጭፈራ በክልሉ ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃ በቱሪስት መስህብነቱ የሚታወቅ ማራኪ የጭፈራ ስልት ነው፡፡ በኮንሶ ዞን የሚገኝ የኮንሶ ዓለም ዓቀፍ ባህላዊ መልክዓ ምድር፣ በጉራጌ ዞን የሚገኝ የጢያ መካነ ቅርስ፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ የቅድመ ታሪክ መካነ ቅርስ ሥፍራ በክልላችን የሚገኙ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ሀብቶቻችን እና አሁን በሚዝገባ ሂደት ላይ የሚገኘውን የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ዕጩ የአለም ቅርስ እና ጥናት የተጀመረለት ወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ ጊፋታን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኙ መስህቦች መገኛ ክልል ነው፡፡
በህዝብና በዞኑ መንግስት የለማው አዲሱ የቱሪዝም መዳረሻ 777 በሀምበርቾ ተራራ ላይና በዙሪያው ያሉ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መስህቦችን ለመጎብኝት እንዲያስችልና የአካባቢውን የቱሪዝም አቅም ለማሳደግ ታልሞ በሀምበርቾ ተራራ ድንቅ የቱሪዝም መስህብ ስፍራ የማህበረሰቡን ባህላዊ ክዋኔዎች አብረው እየከወኑ የሚዝናኑበት የኢኮ ቱሪዝም ስፍራ ነው፡፡
በክልላችን አምስት ብሔራዊ ፓርኮች የሚገኙ ሲሆን ሶስቱ በባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሚተዳደሩ ሁለቱ ደግሞ በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ በፓርኮች ውስጥ በርካታ የዱር እንስሳት በውስጡ የሚገኙ ሲሆን በማጎ ብሔራዊ ፓርክ ዝሆን፣ ጎሽ፣ የቆላ አጋዘን፣ የዱር አሳማ፣ መጋላ ቆርኬ፣ አንበሳ፣ ነብር፣ አቦ ሸማኔ፣ የዱር ውሻና የመሳሰሉት በስፋት ይገኛሉ፡፡
የማጎ ብሔራዊ ፓርክን ለጉብኝት ለየት የሚያደርገው ከዱር እንስሳቱ ባሻገር ማራኪ በሆነ የመልክአ ምድራዊ አቀማመጡ፣ የማጎና የኔሬ ወንዞች ውብ ገጽታዎች፣ ቀልብን የሚስቡ የደን ሽፋን፣ የዱር እንስሳት መፈንጫ የሆኑ ሜዳማ ስፍራዎችና በብሔራዊ ፓርኩ ዙሪያ ያሉ ብሔረሰቦች ባህላዊ የአኗኗር ዘይቤያቸው ከፓርኩ መስህብ ጋር ተጣምሮ ማራኪና ተናፋቂ የጉብኝት ጊዜ እንዲኖር ያስችላሉ፡፡ ማዜ  ብሔራዊ ፓርክ በሀገራችን ኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው የስዌኒ ቆርኬን ጨምሮ አንበሳ፣ የቆላ አጋዘን፣ አቦሸማኔ፣ አምባራይሌ፣ ትልቁ አጋዘንና ፌቆ የመሳሰሉት የሚገኙ ሲሆን ፓርኩ ስያሜውን ባገኘበት የማዜ ወንዝ፣ የቢልቦ ፍል ውሀ፣ በወንዝ ዳር ደንና በተለይ የዱር እንስሳቱን በቀላሉ ማየት የሚቻልበት መሆኑ ቀልብን ይስባል፡፡
ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ከአርባ ምንጭ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡  በብሔራዊ ፓርኩ የሚታወቅበት በርቸሌ የሜዳ አህያን ጨምሮ የስሜኔ ቆርኬ፣ ትልቁ አጋዘን፣ አምባራይሌ፣ የሜዳ ፍየል፣ የናይል አዞና ጉማሬ በስፋት ይገኛሉ፡፡ የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ የዱር እንስሳት የሚርመሰምስበት የነጭ ሳር ሜዳማ ቦታ፣ ቀልብን የሚገዙ የመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ፣ መንፈስ የሚያድሱ የአባያና ጫሞ ሀይቅ ገጽታዎችና በውስጣቸውና በዙሪያቸው በሚገኙ የዱር እንስሳትና አዕዋፋት ዝርያዎች እንዲሁም ከፓርኩ በቅርብት የሚገኘው የደን ሽፍንና አርባ ምንጮች ለጉብኝት ለየት የሚያደርጉት ናቸው፡፡ ሌላኛው ሀብታችን ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ሲሆን በደቡብ ኦሞ ዞንና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በምዕራብ ኦሞ ዞን መካከል የሚገኝ ነው፡፡ በውስጡ ዝሆን፣ ጎሽ ፣ቀጭኔ፣ አቦሸማኔ፣ አንበሳ፣ ቲያንግ የመሳሰሉ የዱር እንስሳት መገኛ ነው፡፡ በፓርኩ በሚገኙ የዱር እንስሳት አይነትና ብዛት፣ በውስጥ በሚገኙ ፍልውሃዎችና ወደ ኦሞ ወንዝ በሚፈሱ ወንዞች፣ ለአይን ማራኪ የሆኑ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥና የኦሞ ወንዝ የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ለጉብኝት ማራኪ ነው፡፡ ጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ በጉራጌ ዞን የሚገኝ ፓርክ ሲሆን ጉማሬ፣ የቆላ አጋዘን፣ አንበሳና የመሳሰሉት እንዲሁም የተለያየ ዝርያ ያላቸው የአዕዋፋት ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡ የጊቤ ብሔራዊ ፓርክ ሀሴትን የሚፈጥሩ የአእዋፋት ዝርያዎች፣ ፍል ውሀዎች፣ አመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞችና ፏፏቴዎች፣ የግልገል ግቤን ተፋሰስ ይዞ የሚታየው እጅግ ማራኪና ቀልብን የሚስቡ አስገራሚ ተፈጥሪአዊ መልክአ ምድርና ዋሻዎች መንፈስን ያድሳሉ፡፡
የክልላችን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ የአርባ ምንጭ አዞ ራንች በአዞ ላይ ለሚደረጉ ሳይንሳዊ ምርምሮችና ጥናቶች አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር፤ የአዞ ቆዳና ስጋ ለአለም ገበያ አቅርቦ ለአገሪቱ የውጪ ምንዛሬ ለማስገኘት፤ ስለ አዞ እርባታ ዘዴ ማስተማሪያ ማዕከል እንዲሆንና ለቱሪዝም የተቋቋመ ነው፡፡ ራንቹ በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛ ሲሆን በዚህም በቱሪዝም ዘርፍ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባሻገር በክልላችን የሚገኙ የቁጥጥር አደን ቦታዎችና የዱር እንስሳት ጥብቅ ቦታዎች ሙርሌ የቁጥጥር አደን ቦታ እና ወልሸት ሳላ የቁጥጥር አደን ቦታ እንዲሁም ታማ የዱር እንስሳት ጥብቅ ቦታ በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ ናቸው፡፡  በተለይ በእነዚህ አከባቢ የሚገኙ ህዝቦች በዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታው ውስጥና አካባቢ የራሳቸው ባህል፣ ዕሴትና የአኗኗር ዘይቤ እና ከአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት ጋር ከፍተኛ ቀርኝት ያለው ባህላዊ ትውፊትና ክንዋኔ ያላቸው መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ጨልቢ በጨው ባህር ዙሪያ በሰሜናዊ የኬንያ ድንበር ላይ የሚገኝ የዱር እንስሳ ጥበቅ ቦታ ሌላኛው ሀብታችን ነው፡፡
ክልሉ ለአዕዋፋት ምቹ መጠለያ በሆኑ ሀይቆች፣ ወንዞችና ጥብቅ ቦታዎች የታደለ ክልል እንደመሆኑ መጠን በአገሪቱ ከሚገኙ የአዕዋፋት ዝርያዎች መካከል ከ1/3ኛ በላይ የአዕዋፋት ዝርያዎች የሚገኙበት ክልል ነው፡፡ በክልሉ የጎብኚዎችን ቀልብ በሚገዙ ብርቅዬ ከሆኑ የአእዋፋት ዝርያዎች ጀምሮ በዓይነት፣ በቀለምና በመጠን የተለያዩ የአእዋፋት ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ ይህም ክልሉን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገር የአዕዋፋት አድናቂ ጎብኚዎች ተመራጭ ክልል እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ከውሃ ሀብቶቻችን የጫሞ ሀይቅ ከአባያ ሀይቅ ጎን ለጎን የሚገኝ ሲሆን ሁለቱን ሀይቆች የሚለየው የእግዜር ድልድይ በመባል የሚታወቀው ተራራ ነው፡፡ የሀሮ ሸይጣን ሀይቅ በስልጤ ዞን የሚገኝ በእሳተ ጎመራ ፍንዳታ የተፈጠረ ሀይቅ ነው፡፡ የኦሞ ወንዝ በማጎና ኦሞ ብሔራዊ ፓርኮች መካከል የሚያልፍ ወንዝ ሲሆን በቱሪስቶች ተመራጭ የሚያደርገው ወንዙ ለጀልባ ስፖርት ምቹ መሆኑና በወንዙ ዙሪያ የተለያዩ የአእዋፍ ዝርያዎች መገኘታቸው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኦሞ ወንዝ በሀገራችን ኢትዮጵያ በመተግበር ላይ ለሚገኙ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች የጎላ ፋይዳ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ በክልሉ የሚገኙ ፏፏቴዎች ክልሉ ተራራማ፣ ሸለቆማ፣ ረባዳማ፣ ሜዳማና የመሳሰሉ መልክአ ምድራዊ ገጽታ ያለው እንደመሆኑ መጠን ለአይን ማራኪ የሆኑና መንፈስን የሚያድሱ በርካታ ፏፏቴዎች በክልሉ ከሚገኙ አብዛኛው ከፍታማ ቦታዎች በደንቅ አወራረድ ቁልቁል ይፈሳሉ፡፡ በክልሉ ከሚገኙ ውብና ማራኪ ፏፏቴዎች በንፋስ ወዲያና ወዲህ እየዋዠቁ ሲወርዱ የሚፈጥረዉ ትዕይንትና ተፈጥሮ ባነጠፈችለት ጥቁር ድንጋይ ላይ እያረፈ የሚፈጥረው ጪስ የጎብኝዎችን ቀልብ ይስባሉ፡፡
ይህንን ሁሉ ሀብት ያለን ቢሆንም የቱሪዝም ሀብታችንን በበቂው ባለማስተዋወቃችን ባለን ዓቅም ልክ እየተጠቀምን አይደለም። ስለዚህ የቱሪስት መስህቦቻችንን በተገቢው በማስተዋወቅ የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግ መስራት አለብን ማለት ነው።  ክልሉ የተፈጥሮ፣ ሰዉ ሰራሽና ታሪካዊ ሀብቶች ባለቤት እንደመሆኑ ይህንን ሀብት ትከረት ሰጥቶ በማልማት፣ በመጠበቅና በማስተዋወቅ ወደ ቱሪዝሙ ገበያ ማስገባት ያሰፈልጋል፡፡ ቱሪዝም ሰፊ የስራ እድል የሚፈጠርበትና የሀገሪቱን መልካም ገጽታ የሚገነባ ዘርፍ ነዉ፡፡ ስለሆነም ሀብቶቻችንን በተገቢ በማልማት ከአግልግሎት ሰጪ ተቋሞቻችን ጋር በማስተሳሰርና ሳቢ የሆነ የማስተዋወቅ ስራዎችን በተለያየ መልኩ በመስራትና ከሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ዉጪ ተደራሽ በማድረግ ቱሪስቶች ወደ ክልላችን በመሳብ የቆይታ ጊዜያቸዉም አንዲራዘም ለማድረግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጠንካራ የሆነ የባለድርሻ አካላት ቅንጀትና ትኩረት ይሻል፡፡
በመሆኑም በ2014 ዓ.ም በተሰራው ስራ ከ3.9 ሚሊየን በላይ ጎብኝዎች ክልላችንን የጎበኙ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ29 ሺህ በላይ የውጪ ሀገር ጎብኝዎች ናቸው፡፡ በ2015 ዓ.ም ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችን ቁጥር ወደ 5.5 ሚሊየን ለማድረስና የውጪ ሀገራት ጎብኝዎችን ቁጥር ወደ 75 ሺ ለማሳደግ ይሰራል፡፡
በክልላችን ያለውን የቱሪስት ቆይታ ጊዜ ለማሳደግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን ይህም ሊሳካ የሚችለው የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የቱሪስት ዝውውር ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተለይም ከሆቴሎች ውጭ ተለይቶ የሚታሰብ አይደለም፡፡ በክልሉ በጉብኝትና በሌሎች ምክንያት ወደ ክልሉ ለሚገባው ቱሪስት የመኝታ፣ የምግብና መጠጥ፤ የመዝናኛ እንዲሁም የማስጎብኘት አገልግሎት የሚሰጡ ብቃት ያላቸዉ በርካታ ተቋማት ይገኛሉ፡፡ አለም አቀፍ መስፈርት አሟልተዉ የኮከብ ደረጃ የተሰጣቸዉ 17 ሆቴሎችና ሪዞርቶች ያሉ ሲሆን በተጨማሪም በከተሞችና በቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች የተገነቡ ሌሎች ደረጃቸዉን የጠበቁ በቱሪስቱ ተመራጭ የሆኑ ሎጆች፣ ሆቴሎች፤ ሪዞርቶች፤ ፔንሲዮኖች፤ ሞቴሎች ወዘተ ከተሟላ መስተንግዶ ጋር አገልግሎት በመስጠጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም በስነ-ምግባራቸዉ የታነጹ በክልሉ በሚገኙ የቱሪዝም መስህቦች ላይ በቂ እዉቀት ያለቸዉ መስፈርቱን አሟልቱ ህጋዊ እዉቅና ያገኙ ከአስራ ሰባት በላይ የሚሆኑ የአከባቢ አስጎብኚ ማህበራት ቱሪስቱን በማስጎብኘት ላይ ይገኛሉ፡፡ በክልሉ የሚገኙ ሆቴሎችና ሪዞርቶች በቂ ስላይደሉ በሆቴልና ቱሪዝም መስክ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ክልሉ አስፈላጊውን እገዛ የሚያደርግ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለፅ እወዳለው፡፡
በመጨረሻም ለቱሪዝም ቀን ስኬት አሻራ ያሳረፋችሁ አካላት፣ የቢሮው ማናጅመነትና የቱሪዝም ዘርፍ ሰራተኞች፣ ከሁሉም ሚዲያ የተገኛችው ጋዜጠኞች፣ ሾፌሮች፣ የክኔት ቡድን አባላት፣ ጉብኝት በተደረገባቸው ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌ የሚትገኙ የመንግስት አካላትና መላው ማህበረሰብ በተለይም የማዜ ብሔራዊ ፓርክና የጎፋ ዞን አመራርና ህዝብ እጅግ ላቅ ያለ ምስጋና እያቀረብኩ የዕለቱ መርሃ ግብር መጀመሩን አበስራለው አመሰግናለው፡፡
 

Leave a comment

Filtered HTML

  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Allowed HTML tags: <a> <em> <strong> <cite> <blockquote> <code> <ul> <ol> <li> <dl> <dt> <dd>
  • Lines and paragraphs break automatically.

Plain text

  • No HTML tags allowed.
  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Lines and paragraphs break automatically.