ዓለም አቀፍ የአፍ መፍቻ ቋንቋቀን በዓለም ለ22ኛ በሀገርአቀፍ ለ12ኛ እንዲሁም በክልላችን ደረጃ ለ3ኛ ጊዜ በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ ላይ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ‹‹ልሳነ ብዙነት ለአገራዊ መግባባት›› በሚል መሪ ቃል በተከበረበት ወቅት የአፍ መፍቻ ቋንቋ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋቸውን የመጠቀምና የማልማት መብታቸውን ተግባራዊ በማድረግ ለዕርቅና ሰላም ግንባታ እንዲሁም ለዘላቂ ልማት ግንባታ እገዛ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ሀብታሙ አበበ ተናገሩ፡፡
አክለውም በሀገራችን ከ80 በላይ ቋንቋዎች መኖራቸውን አውስተው እነዚህን በማልማት፤በመጠበቅና ለሌሎች እንዲተላለፉ በማድረግ ከትምህርት ተቋማት ጀምሮ ሁሉም ለቋንቋዎች ልማት የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በሀገር በቀል ዕውቀት ዙሪያ ምርምር እየሰራ በመሆኑ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ለማልማት የሀዲይሳና ከምባቲሳ ቋንቋዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ ስርአተ ትምህርት በመቅረጽ በማስተማር ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ፕሬዝደንቱ እንዳሉት ለቋንቋና ባህል ጥናት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የባህል፤የታሪክና ቋንቋ ጥናቶች በኢኒስቲትዩት ደረጃ በመክፈት እየተሰራ ሲሆን ማንኛውም ሰው ቋንቋን በቀላል ዘዴ መማር የሚችልበትን ባለ ሶስት ልሳነ ቋንቋ መማሪያን መጽሐፍ፤ሞባይል አፕልኬሽን፣ድረ-ገጽና ሲዲ ተዘጋጅቶ ለተጠቃሚዎች ተሰራጭተዋል፡፡
ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ለቋንቋ መማሪያ ያዘጋጀው ይኸው ዘዴ በሚኒስቴር መ/ቤቱና በሌሎች አካላት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች ዕውቅና መሰጠቱን ጠቁመው ለቋንቋ፤ለባህልና ቅርስ ትኩረት በመስጠት በርካታ ስራዎች ተዘጋጅተዋል ካሉ በኋላ ለትምህርት ክፍሎች ማስተማሪያ ጭምር የሚሆኑ የሚዳሰሱ ቅርሶችን በማሰባሰብ ለሙዚየም አገልግሎት እንዲውሉ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የሚኒስተሩ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ መሀመድ እንደተናገሩት ቋንቋ የማንነት፤የብዝሀነትና የዕምነት እንዲሁም የሌሎች በርካታ እሴቶች መገለጫ በመሆኑ ህዝቦች ታሪካቸው፣፣ልማዳቸው፣ዕምነታቸው፣የህይወት ትውስታቸው ሀገር በቀል ዕውቀታቸውና ሌሎች በርካታ መለያ የሆኑ አስተሳሰባቸውን የሚገኙበት መሳሪያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባት በመሆኑ ሚኒስቴር መ/ቤቱ እነዚህን ለማልማትና ለመምራት የሚያስችል የቋንቋ ፖሊሲ በሚ/ሮች ም/ቤት ታይቶ ስራ ላይ ውሏል ብለዋል፡፡
አክለውም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ሌሎች አካላት ከሚ/ር መ/ቤቱ ጋር በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበው በአሁኑ ወቅት ህገ መንግስቱ ለቋንቋዎች በሰጠው ዕውቅና ህዝቦች ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ማልማት በመቻላቸው ስኬቶች ተመዝግበዋል።
በሀገራችን 53 ቋንቋዎች ፊደል ተቀርጾላቸው ሥራ ላይ የዋሉ ሲሆኑ አፋርኛ፤ትግርኛ፤ሶማሊኛና ኦሮምኛ የክልል የስራ፤የሚዲያና የከፍተኛ ት/ት ቋንቋ መሆናቸውን ተወካዩ አውስተው ከዚህም በተጨማሪ የቋንቋ ፖሊሲው ከአማርኛ በተጨማሪ ሀገራዊ የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ እውቅና ሰጥቷል ብለዋል፡፡
በዚሁ የአፍ መፍቻ ቋንቋ በአል ላይ የሀገራችን የቋንቋ ፖሊሲን ጨምሮ የቋንቋና የህዝቦች ተጠቃሚነት የክልሉን ቋንቋዎች ደረጃን የሚዳስሱ ጥናቶች እና ሌሎች የአፍ መፍቻ ቋንቋዎችን የሚመለከቱ አዝናኝና አስተማሪ ዝግጅቶች የሚቀርቡ ሲሆን የአፍ መፍቻ ቋንቋ በ1948 ፓኪስታን ውስጥ የቤንጋሊ ቋንቋ መማሪያችን ይሁን ብለው መብታቸውን በጠየቁ ተማሪዎች ላይ የጸጥታ ሀይሎች በተኮሱት ጥይት አራት ተማሪዎች መሞታቸውን ምክንያት በማድረግ እየተከበረ መሆኑን የዘገበው የቢሮው መ/ኮ/ዳይሮክተሬት ነው፡፡
በግዛቸውገ/ማሪያም

Leave a comment