
የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ መልዕክት፣
የደቡብ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የክልሉን ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህል ፣ታሪክ ፣ ቋንቋና ቅርስ እንዲሁም ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ መስህቦችን በማልማት ፣በመጠበቅ እና በማስተዋወቅ በየዘርፉ ውጤታማ የሚያደርጉ ተግባራትን በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን ለዚህም ሀገራዊ፣ ክልላዊ እና ተቋማዊ ግብ ጥሎ እየሰራ ይገኛል፡፡
በክልሉ የሚገኙትን መልካም ዕሴቶቻችን ለማሳደግ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት በመስጠት ህዝባችን ከተያያዘው ድህነት፣ ኋላ ቀርነትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ለማላቀቅ የሚያደርገውን ሁሉን አቀፍ ጥረት ለማጎልበት መንግስትና ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በተለየ በቅንጅት እየሰሩበት ያለ በመሆኑ በየዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራት በተቀመጠለቸው የአሰራር ሥርዓትና ማዕቀፍ በመተግበር ለሚያጋጥሙ የአሰራር ክፍተቶች ተገቢውን ምላሽ እና የመፍተሄ አቅጠጫ ማበጀት አስፈላጊነቱ የጎላ ነው፡፡
የክልሉ መንግስት ትኩረት ከምሰጠቸው ሁሉን አቀፍ የለውጥ ሥራዎች አንዱ የክልሉን ህዝቦች የቱባ ባህል ዕድገትና ውጤታማነትን ማራጋገጥ ሲሆን ክልሉ በርካታ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ያሉት በመሆኑ እንደየ ብዝሀነታቸው መጠንና ልክ የብሄረሰቦቹ ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ የባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ሀገረ-ሰባዊ ሥነ-ቃል፣ ባህላዊ የቤት አሠራር፣ አመጋገብ ፣ ባህላዊ አለባበስ ፣ ባህላዊ የመገልገያ ቁሳቁሶች፣ ሥነ-ጥበባዊ ሀብቶች ወዘተ ያላቸው መሆኑ ይጠቀሰሉ፡፡
በክልሉ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡት ቅርሶች መካከል የጥያ ትክል ድንጋይ ፣የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ፓሊዮ አንትሮፖሎጂካል እና የኮንሶ ባህላዊ መልክዓ-ምድር መካነ ቅርሶች የሚገኙበት እንዲሁም በዩኔስኮ በጊዜያዊ የቅርስ ማህደር የተመዘገበና በቅርቡ በቋሚነት እንደሚመዘገብ የሚጠበቀው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ዕጩ የዓለም ቅርስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በተመሳሰይ በክልሉ በርካታ ባህላዊ ክዋኔዎች የሚካሄዱበት የዘመን መለወጫና የመስቀል በዓላት ለአብነትም (ደራሮ፣ያሆዴ፣ጊፋታ፣ ዮ መስቀላ፣ መሳላ፣ ወዘተ…ተጠቃሽ ናቸው። ከሀገር በቀል ዕውቀትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ እንዲሁም ታሪካዊ መዳረሻዎችን በሚመለከት የኮንሶ ብሔረሰብ ባህላዊ መንደሮች እና ባህላዊ እርከን ፣ የዶርዜ ማህበረሰብ ባህላዊ መንደርና የሸማ ሥራ፣ የየም ብሔረሰብ ባህላዊ መድኃኒት ለቀማ፣ በሀመር ብሔረሰብ ዘንድ የሚከወነው ኢቫንጋዲ እና የከብት ላይ ዝላይ፣ በቦዲና ሱርማ ብሔረሰቦች የሚተገበረው የዱላ ምክክቶች፣ የተለያዩ የብሄር ብሄረሰቦች ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች እና አልባሰት እንዲሁም ሌሎች በርካታ ጥነትና ምርምር የሚያስፈልገቸው ቅርሶች እና ሀብቶች መገኛ ነው፡፡
ክልላችን በርካታ የቱሪዝም መደራሻዎችና የተፈጥሮ ሀብቶች ያሉበት ሲሆን ከእነዚህ በዋናነት በውስጣቸው የተለያዩ ብርቅዬ የዱር አራዊት እና የአዕዋፋት ዝርያዎች የያዙ ብሔራዊ ፖርኮች ለአብነት ማጎ፣ ማዜ፣ ነጭ ሳር እና ጊቤ ሸለቆ ብ/ፓርኮች) ፣ በአገራችንም ሆነ በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛ የሆነው የአርባ ምንጭ አዞ ራንች፣ የዱር እንስሳት ጥብቅ ቦታዎች፣ የተፈጥሮ ጥብቅ ደኖች፣ ከ6000 በላይ የሚሆኑ ትክል ድንጋዮች (ጥያ፣ ቱቲ ፈላ፣ ጨልባ ቱቲቲ፣ ሴዴ፣ ሳካሮ ሶዶ፣ ዞፍካር፣ አሰኖ ፣ ገነሜ. .ወዘተ.. የትክል ድንጋይ መካነ ቅርሶች) ፣ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ዋሻዎች ይገኙበታል፡፡
ክልሉ በተመሳሰይ ይርጋ ጨፌ ኦርጋኒክ ኮፊ፣ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች (አባያና ጫሞ)፣ ፏፏቴዎች ፣ ፍል ውሀዎች ውብና ማራኪ መልክዓ-ምድሮች፣ ተራሮች እና ሰንሰለታማ ተራሮች፣ የእግዜር ድልድዮች፣ አርባ ምንጮች፣ የጫሞ አዞ ገበያ፣ ሀሮሸይጣን እና መጨፈራ ሀይቆች እና ሌሎችም በርካታ ወንዞችና ጅረቶች መገኛ ነው፡፡
ክልሉ በባህል፣በቱሪዝምና ሆቴል፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን ልማት፣ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሉበት በተፈጥሮ የታደለ ክልል በመሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎበኚዎች እንዲበረታቱ ለማድረግ ሰላም እና መረጋገት፣ የህዝቦች ትስስርና አንድነትን ማጎልባት እንዲሁም የቱሪስት መዳራሻዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም የመዳረሻዎችን መሰረተ ልማት ማሟለት ወሳኝ ሲሆኑ ለዚሁም ውጤታማነት በየዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላት ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በማጠናከር በአንጻሩም የህዝቦችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደምንሰራ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡
አቶ ሀይለማሪያም ተስፋዬ
የደቡብ ብ/ብ/ህዝቦች ክልል መንግስት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ